እጅን መታጠብ: ሐበሻን ጀርም አይገድለውም?

በብርሃኑ ኃ/ሚካኤል (ሐኪም)

“እነዚህ ሐኪሞች ደግሞ 10 ጊዜ በሳሙና ታጠቡ እያሉ ቆዳችንን አሳሱት እኮ…ከሳሙና ፋብሪካዎች ጋር ሼር ሳይኖራቸው አይቀርም” የሚል ቅሬታ የምታቀርብ የላይ ሰፈር ልጅ አትጠፋም፡፡ የታች ሰፈር ልጆች ደግሞ “ሐበሻ ከምግብ በኋላ እንጂ ከመብላቱ በፊት ብዙም መታጠብ አይወድም” እያሉ ህዝቡን ያሙታል፡፡ ቢታጠብም ለአመል ያህል ነካ ነካ ነው፡፡ “እስኪ የጣት ዉኃ አምጪ…” ነው የሚሉት እመቤቲቱ፡፡ የጣት ዉኃ ከሳሙና ጋር የሚቀርበው ከተበላ በኋላ እርዱን ወይም በርበሬዉን ከጥፍር ለማስለቀቅ እንጂ ከምግብ በፊት ማን እጁን ይፈትጋል? ብዙ ምግብ ቤቶች ወጪ ለመቀነስ ይሁን በሌላ ምክንያት አይታወቅም ሳሙናን ከመታጠቢያ ቦታ ገለል የማድረግ ሱስ ተጠናውቷቸው እናያለን፡፡

እስኪ ለአፍታ እጃችን በቀን ዉስጥ የሚሠራውን ሺ ተግባራት እናስብ፡፡ የጋራዥ ሠራተኛ ብቻ ነው እጁን እሽት አድርጎ መታጠብ ያለበት ያለው ማነው? 

  • ከታክሲ ወያላ የተቀበልናቸውን ያረጁ የአንድ ብር ኖቶችን እናስብ፤ ስንት ሺ በላብ የራሱ መዳፎች እንደነኳቸው መገመት ትችላላችሁ?
  • ከተማ አውቶቡስ ቆመን ስንሳፈር ሚዛናችን ለመጠበቅ የሚረዳንን የቁም የብረት ዘንግ ለምን ያህል ጊዜ እንደጨበጥነው እናስብ፡፡ ምናልባት ያን የብረት ዘንግ በቀን ዉስጥ አንድ ሺ የሚኾኑ ተሳፋሪዎች ላብ ባራሰው እጃቸው ጨብጠውታል፡፡
  • በቀን ዉስጥ የጨበጥናቸው ሰዎች ብዛት ምን ያህል ይኾን? 
  • የኪስ ቦርሳችንን ከኋላ ኪሳችን ስናወጣ ቦርሳው መቀመጫችን ስር እንደነበርና በተቀመጥን ጊዜ ሁሉ በፍትጊያ ዉስጥ እንደነበር አስበዋል? 

ታዲያ ከዚህ ሁሉ የእጅ ተግባር በኋላ በዚያው መዳፍ እንጀራ ጠቅልሎ መጉረስ አይሰቀጥጥም? ምናልባት ሀበሻ ከጀርም በላይ ምች ስለሚፈራ ይሆናል፣ ከምግብ በኋላ እጅና አፉን በሳሙና ፍትግ አድርጎ የሚታጠብ፡፡ ከምግብ በፊት ያልታጠበ ሰው ጀርምን በእንጀራ ጥርግ አድርጎ እየበላ እንደሆነ አይገነዘበውም፡፡ መዳፋችን ብቻ አይደለም ደግሞ ጉድ የሚሰራን፡፡ ንጹህ ናቸው ብለን የምናስባቸው ነገሮች የጀርም መጠለያ ኾነው ተገኝተዋል፡፡ ለመኾኑ ከመታጠቢያ ቤት መቀመጫ የበለጠ ጀርሞች የሚገኙባቸው ዕቃዎችና ሥፍራዎች እንዳሉ ያውቃሉ?  ይህ አስገራሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ብዙዉን ግዜ ጀርሞች ይገኙባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ ቦታዎች እንደ መጸዳጃ ቤትና የቆሻሻ ገንዳ ያሉ በጉልህ የሚታይ ሥፍራዎችን አድርገን ስለምናስብ ነው፡፡ በየቀኑ የምንጠቀምባቸውን እንደእጅ ቦርሳ፤ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ የቲቪ የርቀት መቆጣጠሪያ እና የመሳሰሉትን እምብዛምም የሚገባቸውን ንጽህና አናደርግላቸውም፡፡ ልብ ልንል የሚገባው ግን እጅግ “ንጹህ” ብለን የምንፈርጃቸው የቤት እቃዎችና የግል መገልገያዎች ከመጸዳጃ ቤት የበለጠ የጀርሞች አየር ማረፊያ ኾነው መገኘታቸው ነው፡፡ ጥቂቶቹን ቀጥለን እንመልከት፤

የሴቶች ቦርሳ 

ልብ የማንላቸው በእጃችን ለመንካት የማንደፍራቸውን እንደ ህዝብ ማመላለሻ መኪና ወይም ደግሞ መታጠቢያ ቤት መሬት ላይ ቦርሳዎችን ማስቀመጥ እናዘወትራለን፡፡ በምግብ ጠረጴዛ እና መደርደሪያ ላይ ቦርሳችንን እንደነገሩ ጣል እናደርገዋለን፡፡ ከዚያም ደግሞ አንግበነው እንነሳለን፤ ይህ ተግባር ባክቴሪያ እና ጀርሞችን በነጻ “ሊፍት” እየሰጡ እንደማጓጓዝ ይቆጠራል፡፡

ብዙ ግዜ በቦርሳ ውስጥ የሚገኙ የእጅ ቅባት ፤ ሊፒስቲክ እና ማስካራም በእጅ በመነካካት እንደሚበከሉ እና ወደ ቤት ውስጥ ጀርም እና ባክቴሪያን ይዘው እንደሚገቡ ይጠቁማል፡፡ ቦርሳዎችን ሆነ ብለን ስለማናጸዳ እና የተለያዩ የቦርሳዎችን ክፍል በእጃችን ስለምንነካካ ጀርምን የማስተላፍ አደጋው ከፍ ያለ ነው፡፡ የእጅን ንጽህና መጠበቅ እና ቦርሳዎችን በማጽዳት በባክቴሪያ የመበከል እድልን መቀነስ ይቻላል

ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች (smart phones and tablets) 

እጃችንን መታጠቢያ ቤት በገባን እና በወጣን ቁጥር መታጠብ ባንረሳም በየቀኑ የምንጠቀምባቸውን ዘመናዊ ስልኮቻችንን ከመንካታችን በፊት ግን መታጠብን አናስታውስም፡፡ ማይክሮባዮሎጂስቶች እንደ ኢ.ኮሊ ያሉ በሽታን የሚያመጡ ባክቴሪያዎች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ከሰላሳ ስልኮች እና ሰላሳ ታብሌቶች ላይ ናሙና በመውሰድ ባደረጉት ጥናት መሰረት በአማካኝ አንድ ስልክ 140 ዩኒት እንዲሁም አንድ ታብሌት 600 ዩኒት የባክቴሪያ ስታፍይሎከስ ኤረስ (ስታፍ) ከየአንዳንዱ ናሙና ላይ ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህንን ቁጥር በአማካኝ አንድ ዘመናዊ መታጠቢያ ቤት ውስጥ ከሚገንኝ የባክቴሪያ መጠን ጋር ስናነፃፅረው ግን የሚያስገርመው በአንድ ናሙና 20 ዩኒት ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከ 20- 10000 ዩኒት bacteria ለጤና ጠንቅ ነው፡፡ 

“በምግብ ቤቶች ውስጥ ከሚሰሩ ሰራኞች እጅ ላይ በሚወሰድ ናሙና ይህንን ያህል የባክቴሪያ መጠን ብናገኝ ከስራቸው ተወግደው በመሰረታዊ ንጽህና አጠባበቅ ዙሪያ ስልጠና እንዲወስዱ ሊደረግ ይችላል፡፡ ነገር ግን 600 ዩኒት የሚያህል ከፍተኛ መጠን ያለው bacteria በተለያዩ የፕላስቲክ መገልገያዎች ላይ ይዘን እንገኛለን፡፡”

ስፓንጅ

እቃዎቻችንን ከቆሻሻ እና ከጀርሞች ለማጽዳት የምንጠቀምበት ስፖንጅ እራሱ በቤት ውስጥ ከምንጠቀምባቸው ቁሳቁሶች ውስጥ ዋነኛው የባክቴሪያ ተሸካሚ መሆኑ አይገርምም፡፡ አንድ ኢንች በአንድ ኢንች በሆነ ስፖንጅ ላይ በአማካኝ ከአስር ሚሊዮን ያላነሰ የባክቴሪያ መጠን ሲገኝ የዚሁ አንድ አራኛ መጠን ብቻ በመታጠቢያ ቤቶች መቀመጫ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንንም የሚያባብሰው ሰዎች እስፖንጆቻቸውን ቶሎ ቶሎ ለመቀየር አለመሞከራቸው ነው፡፡ እስኪ ራስዎን ይጠይቁ፤ እርስዎም እንዲህ አይነት የጀርሞችን መጠን የሚያስተናግድ ስፓቦጅ ተጠቃሚ እንደሆኑ ከጠረጠሩ አሁኑኑ አስወግደው በአዲስ ስፖንጅ ይተኩ፡፡

የእቃ ማጠቢያ ገንዳ 

ብዙዎቻችን መታጠቢያ ቤቶችን እንደዋነኛ የጀርም መደበቂያ ቦታ አድርገን ብንቆጥርም በትክክል ግን መጨነቅ የነበረብን ስለ ኩሽናዎቻችን ነው፡፡  እንደ ስፖንጆች ሁሉ የኩሽና እቃ ማጠቢያ ገንዳዎች ከመታጠቢያ ቤቶች መቀመጫ  የበለጠ የጀርሞች መቀመጫ ናቸው፡፡ የ2011 ኤን.ኤስ.ኤፍ አለም አቀፋዊ የቤት ውስጥ የጀርሞች ጥናት እንደሚያሳየው ካሉ የእቃ ማጠቢያ ገንዳዎች ውስጥ አርባ አምስት በመቶ የሚሆኑት እንደ ኮሊፎርም፤ ሳልሞኔላ እና ኢ.ኮሊ ላሉ ባክቴሪያዎች መቀመጫ ናቸው፡፡ እነዚሁ የባክቴሪያ ዓይነቶች በሰላሳ ሁለት በመቶ የሚሆኑት የእቃ መደርደሪያዎች ላይ እንዲሁም አስራ ስምንት በመቶ የሚሆኑት መክተፊያዎች ላይ ተገኝተዋል፡፡

የቪዲዮ ጌም/የቴሌቪዥን የርቀት መቆጣጠሪያዎች

በዩኒሴፍ እና ዩኒሊቨር በተደረገ ጥናት መሰረት መቶ ሴንቲ ሜትር በመቶ ሴንቲ ሜትር በሆነ የቴሌቪዥን የርቀት መቆጣጠሪያ ላይ በአማካኝ 1600 ባክቴሪያ ሲገኝ በቪዲዮ ጌም መቆጣጠሪያ ላይ ደግሞ በአማካኝ 7863 ባክቴሪያ ይገኛል፡፡ በዚሁ የስፋት መጠን የመታጠቢያ ቤት መቀመጫ ላይ ግን 1600 ብቻ ባክቴሪያ ይገኛል፡፡ እንግዲህ እነዚህን ቁጥሮች ብዙውን ሰአታቸውን ቪዲዮ ጌም በመጫወት  የሚያሳልፉት ወጣቶች ከመታጠቢያ ቤት ሲወጡ እጃጨውን መታጠብ ከመዘንጋታቸው ጋር ደምረው ያስሉት – አደገኝነቱ የከፋ ነው፡፡

ኪ ቦርድ

የግል ኮምፒውተሮችም ላይ ቢሆን ብዙ አይነት ባክቴሪያዎች ይራባሉ፡፡ በኪቦርድ ስንጥቆች እና ቀዳዳዎች ውስጥ የሚገባውን ቆሻሻ ማጽዳት ከባድ ነው፡፡ ከባድ ቢመስልዎትም በባክቴሪያ ላለመበከል ቢያንስ በወር አንድ ግዜ ኮምፒውተሮችዎን አጠፋፍተው ኪቦርድዎን ማጽዳት ይልመዱ፡፡

የሻወር ውሀ ማፍሰሻዎች

ሙቅ ውሀን የሚያፈሱ የሻወር ቤት የውሀ መውረጃዎች ውስጣቸው በሚቀረው እርጥበትን ያዘለ ሙቀት የተነሳ ቀላል የማባይባሉ የጀርም መሰብሰቢያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

የሻወር ውሀ ማፍሰሻዎች ከበሽታ አምጪዎች ነፃ ለማድረግ እቃውን ይፈታቱ እና ውስጥ በጎርጓዳ ሰሀን ውስጥ አድርገው በፈላ ቪኔጋር ይቀቅሉት፡፡ በተጨማሪም የሻወር ውሀ መፍሰስ እንደጀመረ በፍጥነት ወደ ፊትዎ ውሀውን አያፍስሱ፡፡

Total Page Visits: 965 - Today Page Visits: 2

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *