በኃላፊነት ይጠጡ???

በ21ኛው ክፍለዘመን “በሀላፊነት ይጠጡ” የሚለው አባባል በብዙ ሰዎች እንደ መርህ ይታያል፡፡ የብዙ ቢራ አምራቾች የማስታወቂያ ማሳረጊያ ኾኖም ያገለግላል፡፡ በዓለም የጤና ድርጅት የካንሰር ጥናት ኤጀንሲ በተደረገው የ2014ቱ የዓለም የካንሰር ሪፖርት መሰረት ግን ምንም ያህል የአልኮል መጠን ለካንሰር አደገኛ እንደሆነ ነው የሚያትተው፡፡ መጠኑ ምንም ይሁን ምን አልኮልን መጠቀም ከምግብ መውረጃ ቧንቧ ካንሰር በተጨማሪ እንደ ጡት ካንሰር ካሉ እጢዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው የቅርብ ዓመታት ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ የጠንካራ አልኮል መጠጥ እውነታዎች እንደ ዶ/ር ሄልም ከሆነ ከአልኮል መጠጥ ጋር ተያያዥነት ያለው ካንሰር የጉዳቱ መጠን የሚወሰነው መጀመሪያ በሚያገኘው የሰውነት አካል ነው፡፡ በዚህም መሠረት መጀመሪያ ጉሮሮ ከዚያም ዝቅ ብሎ ያለውን የምግብ መውረጃ ቧንቧ በዋናነት ያጠቃል፡፡ በሁለተኛ ደረጃም በትልቁ አንጀት የላይኛው እና የታችኛው ክፍል እንዲሁም በጉበት ላይ ያለው አደጋ የሰፋ ነው፡፡ ብዙውን ግዜ የመጠጡ ዓይነት የችግሩን መጠን አይወስነውም፡፡ በምግብ መውረጃ ቧንቧ ካንሰር ግዜ ግን ጠንካራ የአልኮል መጠጦች በውስጣቸው የሚይዙት ኤታኖል የውስጡን ቆዳ በመላጥ የከፋ ጉዳት እንደሚያደርሱ ታውቋል፡፡ መጠጥ እና ሲጋራን ማቀላቀል ሲጋራ ማጤስ ለካንሰር እንደሚያጋልጥ ቀደም ብሎ የታወቀ ሀቅ ቢሆንም ብዙዎች የሚዝናኑበት ሲጠጡ ማጨስ ደግሞ የበለጠ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በኃይል የሚጠጡ እና የሚያጨሱ ሰዎች ለተለያዩ ከአየር እና ምግብ መውረጃ ቧንቧዎች ጋር ለተያያዙ የካንሰር ዓይነቶች ተጋላጭ ናቸው፡፡ ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆኑት የነዚህ ካንሰር ዓይነቶች መጠጥ እና ሲጋራን ባለመጠቀም ብቻ መቅረፍ ይችላሉ፡፡ አልኮልን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ካልቻሉ በኃላፊነት ይጠጡ የሚለውን መርህ ከመከተል የተሻለ አማራጭ አይኖርም፤ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ ይበሉ፡፡ የግለሰብ ጤናማ ባህሪያት፡- 1. ” መጠን አትለፉ” – ይህ የደም ግፊትዎን ፤ የኮሌስትሮል እና የካሎሪ መጠን ከማወቅ ጋር ይመሳሰላል፡፡ መጠን ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ ለአንዱ ብዙ የሚባለው ለሌላው ትንሽ ሊሆን ይችላል፡፡ 2. ወንዶች ከ1.5 (20 ግ) ሴቶች ደግሞ ከ1 (15ግ) መጠጥ የበለጠ አይውሰዱ 3. “ያነሰ የበለጠ ነው ” – ያነሰ አልኮል መጠቀም ለበለጠ ጤና እና ረጅም ዕድሜ መጎናጸፍ ይረዳል፡፡ 4. ” እረፍት ይውሰዱ” በየሳምንቱ ከ1-2 ቀናት ምንም አልኮል አለመጠጣት ጉበትን እንዲያገግም ይረዳዋል፡፡
መንግስት ምን ማድረግ ይችላል? 1. የአልኮል መጠጦችን ዋጋ መጨመር – በተለይም የወጣት ጠጪዎችን ለመቀነስ ሊረዳ ይችላል፡፡ 2. አልኮል መጠጦችንም እንደ ምግብ ሁሉ ልካቸውን በግራም ላያቸው ላይ በመፃፍ ሰዎች ምን ያህል እንደጠጡ እንዲያውቁ መርዳት፡፡ 3. አልኮል መጠጦች የሚሸጡባቸውን ቦታዎች ውስን ማድረግ ለምሳል በየሱቁ እንዳሸጡ ማገድ፡፡ 4. የመጠጥ ሱሰኛ ለሆኑ ሰዎች ከሁኔታው እንዲወጡ በመርዳት እነሱንም ኅብረተሰብንም መጥቀም፡፡ 5. በመጠጥ ሱሰኝነት ዙሪያ ጥናቶች እንዲሰሩ መዋእለ ንዋይ ማፍሰስ፡፡ 6. ለአልኮል መጠጥ ተለዋጭ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮችን በማቅረብ ሰዎች ያለ አልኮል ተፅእኖ እንዲዝናኑ መርዳት፡፡

Total Page Visits: 1959 - Today Page Visits: 3

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *