ስፒና ቢፊዳ ማለት የአከርካሪ መሰንጠቅ ሲሆን ከነርቭ ቱቦዎች መበላሸት የሚመጣ ነው፡፡ አከርካሪ ከ33 የአከርካሪ አጥንቶች ይሰራል፡፡
ስፒና ቢፊዳ ገና በጽንስ ጊዜ የአንድ ወይንም የበለጡ አከርካሪ አጥንቶች ስሪት ትክክል አለመሆን የሚፈጥረው ችግር ነው፡፡ ይህም ደግሞ ነርቮችን ስለሚያጋልጣቸው ዋናውን የነርቨስ ሲስተም ማዕከልን ይጎዳዋል፡፡ የጉዳቱ መጠን ግን እንደ ስንጥቃቱ መጠን እና ወደ ላይኛው የአከርካሪ ክፍል መጠጋት መጠን ይወሰናል፡፡ ሁለት ዓይነት የስፒና ቢፊዳ ዓይነቶች አሉ፡፡ እነሱም፡-
የስፒና ቢፊዳ መንስኤ ምንድን ነው?
የስፒና ቢፊዳ ዋነኛ ምክንያት ባይታወቅም ዘር እና አካባቢያዊ ተፅእኖዎች ምክኒያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡ የእናት በእርግዝና ወቅት የስኳር ህመምተኛ መሆን ወይንም የአልኮል ተጠቃሚ መሆን ፤ በተጨማሪም የሚጥል በሽታ (ኤፒለፕሲ) መድኃኒትን (ለምሳሌ – ቫልፕሮዬት እና ካርባማዜፒን) መጠቀም ከስፒና ቢፊዳ ጋር ተያያዥነት ሊኖራቸው እንደሚችል ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፡፡
በእርግዝና የመጀመሪያ ወራት በአመጋገብ ውስጥ የፎሊክ አሲድ አለመካተት ሌላው ምክኒያት ሲሆን ችግሩም በሴት ሕጻናት ላይ የበለጠ ይስተዋላል፡፡ በስፒና ቢፊዳ የተጠቃ ልጅ ከወለዱ ወላጆች ተመሳሳይ ችግር ያለበት ልጅ የመውለድ 25 በመቶ እድል ሲኖራችው ስፒና ቢፊዳ ያለባቸው ሰዎች ራሳቸው ደግሞ ተመሳሳይ ችግር ያለበት ልጅ የመውለድ 25 በመቶ እድል አላቸው፡፡
ስፒና ቢፊዳ በምን ዓይነት ምርመራ ይታወቃል?
ከ 16-18 የእርግዝና ሳምንታት ውስጥ በሚደረግ የደም ምርመራ የእናቲቱን ሴረም አልፋ ፌቶ ፕሮቲን ከፍ የማለት መጠን በመመልከት ማወቅ ይቻላል፡፡ 98 በመቶ ያህሉ ደግሞ ከ 18-20 የእርግዝና ሳምንት በጽንሱ ላይ የሚደረግ የአልትራ ሳውንድ ምርመራ አማካኝነት ለይቶ ማወቅ ይቻላል፡፡
ስፒና ቢፊዳ ሕክምና አለው?
በስፒና ቢፊዳ የተፈጠረው ችግር ቀላል ከሆነ ህክምና ሳያስፈልገው ይድናል፡፡ ከበድ ያለ ከሆነም በቀዶ ህክምና ሊጠገን ይችላል፡፡ በአእምሮ ውስጥ የሴሬብሮስፓይናል ኖርማል አፈሳሰስ ይረበሻል፡፡ ይህም ሐይድሮስፋለስ የተባለውን ችግር ይፈጥራል፡፡ በዚህም ግዜ ፈሳሹን ለመጥረግ ቀዶ ህክምና ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ የእድገትን እና የእንቅስቃሴንም ችግር ለመፍታት ከቀዶ ህክምና ውጪም በፊዚኦቴራፒ መፍትሄ ሊገኝ ይችላል፡፡ ሽንት የመሽናት ችግር ከተፈጠረ በተለመደው የካቲተር ድጋፍ ሊረዱ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም የስነልቦና ድጋፍና ትምህርት ያስፈልጋል፡፡
የስፒና ቢፊዳ ተጋላጭነትን እንዴት መቀነስ ይቻላል?
ዋናው የመከላከያ መንገድ አንዲት እናት ከማርገዟ አንድ ወር አስቀድሞ እስከ አስራ ሁለተኛ የእርግዝና ሳምንት ድረስ በየቀኑ የፎሊክ አሲድ እንክብል መውሰድ ነው፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ 400 microgram ፎሊክ አሲድ እና
200 ሚ.ግ ወተት በየቀኑ መውሰድ እስከ ሰባ በመቶ የሚሆነውን በስፒና ቢፊዳ የመያዝ እድል ይቀንሰዋል፡፡
እንደ ጎመን ያሉ አረንጓዴ ቅጠል ያላቸው አትክልት፤ ብርቱካን፤ ሽምብራ፡ አተር እና የበሰለ ባቄላ ፎሊክ አሲድን የሚይዙ የምግብ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ታሽገው የሚሸጡ የእህል ምግቦችም (ሲሪየልስ) ፎሊክ አሲድን እንዲይዙ ተደርገው ይመረታሉ፡፡