ራስን መሳት (Concussion) ምንድን ነው?

“ራስን ስለመሳት” መሳት የሌለብዎ ቁምነገሮች

Dr Birhanu H.Michael (MD), Neurosurgeon, Asst. Professor in Neurological Surgeries, Chief of Spine Surgeries Unit

ራስን መሳት በጭንቅላት ላይ በሚደርስ አንዳች ጉዳት የተነሳ የሚከሰት በአእምሮ ውስጥ የሚገኙ የነርቭ ህዋሶች አሠራር መናጋት ነው፡፡  ይህም ማለት የተወሰነው የአእምሮ ክፍል በጊዜያዊነት ሥራውን ያቆማል ማለት ነው፡፡ 

ምልክቶቹም በጊዜዊነት ራስን መዘንጋት ፤ ራስ ምታት እና በአብዛኛው ከአደጋው ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል መርሳት ናቸው፡፡ ማስመለስ እና ማቅለሽለሽም ከተለመዱ ምልክቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በጭንቅላት ላይ በሚደርሱ ግጭቶች ሁሉ አደገኛ የመሆን እድል ቢኖራቸውም ጉዳቱ ኃይለኛ ካልሆነ ግን ውስብስብ ችግር ላያስከትል ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕክምናም ሳያስፈልገው ወቅቱን ጠብቆ በራሱ ጊዜ ይድናል፡፡ 

በኃይለኛ ግጭት ጊዜ ግን የከፋ እና ውስብስብ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡፡  ለምሳሌ ግጭቱ በራስ ቅል ስር የሚገኝ የደም ማመላለሻ ቧንቧን በመበጠስ ደም ቀስ በቀስ ፈስሶ አንድ ቦታ በመጠራቀም አእምሮ ሥራውን እንዳይሠራ ሊያርግ ይችላል፡፡ ደሙ የራስ ቅል ላይ በሚከናወን ቀዶ ሕክምና ካልተወገደ የህመምተኛው ሕይወት ለአደጋ ሊጋለጥ ይችላል፡፡  በከፋ አደጋ ምክንያት ራስን ስቶ ለቀናት መቆየትም በአእምሮ ውስጥ እብጠት የማምጣት እድል ስላለው አደገኛ ነው፡፡    ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሁኔታዎች ሕመምተኛው ላይ ከታዩ ሐኪም ያማክሩ ዘንድ ይመከራሉ፡-

  • ከሁለት ደቂቃ በላይ ራሱን ስቶ ከቆየ፤
  • ራሱን ስቶ ቆይቶ ከነቃ በኋላ እንቅልፍ እንቅልፍ የሚለው ከሆነ እና የንግግር ችሎታው ከተዛባ፤
  • ሁኔታው ከተሻሻለ በኋላ መልሶ የመባባስ ወይም የማገርሸት ነገር ካሳየ፤
  • በተደጋጋሚ ካስመለሰው፤
  • ያልተለመደ የሰውነት እንቅስቃሴ ካሳየ፤

አንድ ሐኪም ራሱን የሳተን ህመምተኛ ወደ ቤት የሚልከው መቼ ነው ?

ራሱን የሳተ ህመምተኛ ሀኪም ቤት በመተኛት የ24 ሠአት ክትትል ሊደረግለት ይገባል፡፡ ነገር ግን ሁኔታው የከፋ ካልሆነ እና መኖሪያው አመቺ ከሆነ የቤት ውስጥ ክትትል በቂ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ ራሱን ለሳተ ሰው ሊደረግ የሚገባ ክትትል በአጠቃላይ ሲታይ ከአደጋው በኋላ ህመምተኛው ከ 12 – 24 ሰዓታት የዘለቀ ክትትል ሊደረግለት ይገባል፡፡ 

በየአንድ ሰዓቱ ልዩነት ለሊትን ጨምሮ ሕመምተኛውን የራሱን ስም ወይም አድራሻ የመሳሰሉ ቀላል ጥያቄዎችን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ቀላል ነገሮች ማስታወስ ካልቻለ በፍጥነት ሐኪም ጋር መውሰድ ያስፈልጋል ፡፡ 

ራስን መሳት ከተከሰተበት ወቅት ጀምሮ መደረግ ያለባቸው ነገሮች 

ብዙውን ጊዜ ራስን መሳት ጋር ተያይዘው የመጡ ችግሮች ቀስ በቀስ ከቀናት በኋላ ይጠፋሉ፡፡ ይህ መሆን እንዲችል መታወስ ያለባቸው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡-

  • አእምሮ ከህመሙ እንዲድን ማረፍ እና ከጭንቀት ነጻ መሆን ይገባዋል፡፡
  • ከብዙ ንባብ እና ለረዥም ሰዓት ቴሌቭዥን ከመመልከት መቆጠብ ይኖርበታል፡፡ 
  • በመጀመሪያዉ ሳምንት ከባድ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ አይኖርበትም፡፡ ከዚያ ይልቅ ብዙ የአካል እረፍት ማድረግ ያሻል፡፡

አእምሮን መሳት ለዘላቂ ጉዳት ሊያጋልጥ ይችላልን? 

የአእምሮ መሳቱ ሁኔታ የከፋ ከነበረ እና በሽተኛው እረፍት ካላደረገ ምልክቶቹ ለወራት ሊቆዩና በአንዳንድ ሁኔታዎችም ዘላቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም በዚህ መነሾ “የሚጥል በሽታ” ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በተለይም ደግሞ ራስን መሳቱ ተደጋግሞ በሚያጋጥም ጊዜ ከሆነ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ በቦክስ ስፖርተኞች  ላይ ይህ ሊከሰት ይችላል፡፡  ይህ ሁኔታ ” ድህረ- ግጭት የአእምሮ ቀውስ” በመባል ይታወቃል፡፡  

ብዙ ህመምተኞች ራስ ምታት፤ ራስ ማዞር፤ ድካም፤ ምቾት ማጣት፤ በድምፅ መረበሽ እና ትኩረት ማጣት ችግሮች ይሰቃያሉ፡፡ የአልኮል መጠጥ መጠቀምም አይስማማቸውም፡፡ እነዚህን ምልክቶች ካስተዋሉ በፍጥነት ሐኪም ማማከር አለብዎ፡፡ 

በአጠቃለይ ሲታይ በእድሜ ያነሱ ህመምተኞች ሙሉ በሙሉ የመዳን እድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ በ “ድህረ- ራስን መሳት” ወቅትም ብዙ ጊዜ ቀለል ያለ ራስ ምታት፤ ራስ ማዞር፤ የመተንፈስ ችግርና የጭንቀት ስሜት በህመምተኛው ላይ ይንፀባረቃል፡፡ ይህ ሁኔታ የአእምሮው ጉዳት ዝቅተኛ ወይም ባዶ በሆነበት ጊዜም የሚያጋጥም ነው፡፡ ማንኛውም በጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ያጋጠመው ግለሰብ በቂ የሕክምና ምርመራ ማግኘት አለበት፡፡ ጉዳቱ ከመጠን ከፍ ያለ ከሆነም ምርመራው በነርቭ ሀኪም ወይንም የነርቭ እና አእምሮው ቀዶ ጥገና ሀኪም መታየት ይኖርበታል፡፡

Total Page Visits: 690 - Today Page Visits: 1

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *