ለመጨረሻ ጊዜ ሐኪም ያዩት መቼ ነበር? 

ይህን ጊዜ በኩራት “ከአምስት ዓመት በፊት” ብለው መልሰው ይኾናል፡፡ ግዴለም አይኩራሩ፡፡ 5 ዓመት አለመታመም ጤንነትዎን አያሳይም፡፡ ይመኑኝ! አምስት ዓመት ለፖለቲካ ምርጫ ካልሆነ ሐኪም ለማየት እጅግ በጣም ሩቅ ዘመን ነው፡፡ እንደገና ልብ ይበሉ! ….አለመታመም ጤንነት አይደለም፡፡ 

የሰው ልጆች በዓመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ ሙሉ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራሉ፡፡ እንኳን ሰው መኪናም ዓመታዊ ምርመራ ያደርግ የለ? ቀላል የሚባሉ እና አጭር ጊዜ የሚፈጁ የጤና ምርመራዎችን በየተወሰነ ጊዜ ማድረጉ ፋይዳው የትየለሌ ነው፡፡ አንደኛ ትናንሽ የሚመሰሉ ግን ስለ ጤናዎ ከሚገምቱት በላይ መናገር የሚችሉ ለውጦችን ያሳያሉ፡፡ በተጨማሪ ድምጽ አጥፍተው ዉስጥ ዉስጡን ጤናዎን እየሸረሸሩ የነበሩ አደገኛ በሽታዎች ብዙ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት እንዲደርሱባቸው ያስችልዎታል፡፡

ስለጤናዎ የሚያስቡ ከሆነ ራስዎን ለጥቂት ደቂቃዎች በመስታዎት አተኩረው በመመልከት ብቻ ብዙ ነገር ሊረዱ ይችላሉ- ዓይንዎ ቀልቷል ? የጥፍርዎ ጫፎች ቡናማ ቀለም አምጥተዋል? ትናንሽ ለውጦችን ማስተዋል ከቻሉ ችግር ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን ለመለየት ያበረታታዎታል፡፡ ይህ ሲባል በትናንሽ ነገሮች ራስን መረበሽ አይገባም፡፡ ምልክቶች ችግር የሚሆኑት ቀጣይነት ሲኖራቸው አሊያም ከሌሎች ምልክቶች ጋር ተቀላቅለው ጉዳዩን ክብደት ሲሰጡት ነው፡፡ ለማንኛውም አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከቱ ሐኪም ያናግሩ፡፡

ከ40 ዓመት በፊት መሸበት

ያለ ዕድሜ መሸበት ከጤና ጋር የተያያዘ ምክንያት ሊኖረው ይችላል፡፡ 40 ዓመት ሳይሞላዎ የፀጉርዎ አጋማሽ ከሸበተ የደምዎን የስኩዋር መጠን ቢመረምሩ አይከፋም፡፡

ሸካራ ሽፍታዎች

ቆዳ ላይ የሚወጡ ጠንካራ ምልክቶች ወይንም ኬራቶሲስ ጠቆር ያሉና ከቤተሰብ የሚወረሱ ሲሆኑ ችግር አያመጡም፡፡በፀሐይ ምክንያት የሚመጣው ክራቶሲስ ግን የካንሰር ምልክት ሊሆን ስለሚችል ቀልጠፍ ብለው ሐኪም ያማክሩ፡፡

የቅንድብ እርዝመት ማጠር

ከቅንድብ ማለቂያ በኩል ፀጉር በመነቀል የቅንድብ እርዝመት ማጠር የታይሮይድ ሥራውን አለማከናወን ምልክት ሲሆን የራስ ፀጉርንም ጭምር ያሳሳል፡፡ ነገር ግን ሕክምና ስላለው ፀጉር በፍጥነት ወደነበረበት መመለስ ይችላል፡፡

የዓይን ቆብ ዝቅ ማለት

የዓይን ቆብ ዝቅ ማለት ከእድሜ ጉዳይ ጋር ላይያያዝ ይችላል፡፡ ምን አልባት ለዓይን ውበት ይሰጣል ብለው ቢያስቡ እንኳ መመርመሩ ያዋጣል፡፡  የዓይን ቆብ በጣም ዝቅ ብሎ እይታን ማበላሸት ደረጃ ከደረሰም በቀዶ ህክምና ከፍ መደረግ ይኖርበታል፡፡

የዓይን ቀለም መለወጥ

ብዙ ጊዜ ደክመዎት አሊያም ከፈሳሹ አብዝተው በማደርዎ ሊሆን ይችላል ዐይንዎ የሚቀላው፡፡ ነገር ግን የዓይንዎ ነጭ ክፍል ቢጫ ከሆነ “ጆንዲስ” የተሰኘው የጤና ችግር  ሊሆን ስለሚችል ሐኪም ያማክሩ፡፡ በተለምዶ የዓይን  መቅላት የምንለው በህክምናው “ኮንጃክቲቫይተስ” ይባላል፡፡ ይህም የሚቀጥል ከሆነ የ”ክላሚዲያ” ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  

የጆሮ ጫፍ መጨማደድ

የአሜሪካ የሕክምና ጆርናል እንዳሳተመው ከሆነ የጆሮ ጫፍ ስላሽ መታጠፍ የልብ ህመም ተጋላጭነትን በአንድ ሦስተኛ ይጨምረዋል፡፡ ሁለቱም ጆሮዎት ከሆኑ ደግሞ ቁጥሩን ወደ 77 ፐርሰንት ከፍ ያደርገዋል፡፡ የጆሮዎ መታጠፍ የሚያሳየው የመለጠጥ ችሎታን ማነስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በደም ማመላለሻ ቧንቧዎችም ላይ ይንጸባረቃል፡፡ አንድሪው ዌይል የተባለው የአሜሪካ ቀዳሚ የጤና ባለሙያ እንደሚያስረዳው ከሆነ “አንዳንድ ጊዜ ይህ ከእርጅናም ጋር ተያይዞ ይመጣል፡፡ የልብ ህመም ተጋላጭነትም ከእድሜ መጨመር ጋር አብሮ የሚጨምር ነገር ነው፡፡”

የጉንጭ መቅላት

ዕድሜያቸው ከ 30-55 ዓመታት በሆኑ ሴቶች ላይ በብዛት የሚከሰተው የጉንጭ እና የአፍንጫ መቅላት በንዴት ወይንም ጭንቀት፤ለፀሐይ እና ለሚያቃጥል ምግብ በመጋለጥ የደም ስሮች በመስፋታቸው የሚከሰት ስለሆነ ከእነዚህ ሁኔታዎች ይራቁ፡፡ ይህ ሁኔታ በዓይን ላይ ሲከሰት ከሌላ “ሉፐስ” ከተሰኘ ችግር ጋር ሊደናገር ስለሚችል ሐኪም ያማክሩ፡፡   

የከንፈር መሰንጠቅ

የከንፈር ከዳር እና ዳር መሰንጠቅ አንዳንዴ የቫይታሚን “ቢ” ወይንም ዚንክ እጥረት ሊሆን ይችላል፡፡ በጣም ለረጅም ጊዜ ተሰንጥቆ ከቆየም የፋንገስ ኢንፌክሽን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ለአፍ እና ለጉሮሮ ህመም የሚደረገው ተመሳሳይ ሕክምና ለዚህም ሊረዳ ይችላልና ሐኪም ይጎብኙ፡፡

የአንገት እብጠት

የአንገት አካባቢ እጢዎች በአንድ ለሊት አብጠው ቢያድሩ ማስተዋልዎ አይቀርም፡፡ እንቅርት ግን ቀስ በቀስ እያደገ ስለሚሄድ ላይስተዋል ይችላል፡፡ ይህ ባብዛኛው ዕድሜያቸው ከ 20-50 ዓመት በሆኑ ሴቶች ላይ የሚያጋጥም ነው፡፡ ከእብጠቱ በተጨማሪ ዓይን ወጣ ወጣ ካለና የክብደት መቀነስ ከኖረም የዚህ በሽታ ተጨማሪ ምልክቶች ናቸው፡፡

የቆዳ መጥቆር 

ፀሐይ ባያገኞትም ቆዳዎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠቆረ ከመጣ ሀኪም ማማከሩ አይከፋም፡፡ በተለይም ደግሞ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የድካም ፤የህመም እና የማሳከክ ምልክቶች ካሉ “አዲሰንስ” የተባለ በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ጥሩነቱ ይህ ችግር በሕክምና መዳን መቻሉ ነው፡፡

ሽፍታ

የማይለቅ እና እንደ ዶሮ ቆዳ የመሰለ ሽፍታ በተለይም በእጆች አካባቢ ከሦስት ሰው በአንዱ ላይ የሚገኝ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ምንም ዓይነት ጉዳትም አያመጣም፤ ነገር ግን እርስዎ ሽፍታውን ማጥፋት የሚሹ ከሆነ  በወተት ውስጥ የሚገኘው አሚኖ አሲድ ሊረዳ ስለሚችል የገላ መታጠቢ ገንዳ ውስጥ ወተት በማድረግ እና ሳሙናነት በሌለው የገላ መታጠቢያ መታጠብ ይጠቅማል፡፡  በድንገት ከተባባሰ ግን ሀኪም ቢያማክሩ የስቴሮይድ ቅባት ሊያዝልዎ ይችላል፡፡

የመዳፍ መቅላት

የመዳፍ ማሳከክ ሲሳይ ሊኾን ይችላል፤ የመዳፍ መቅላት ግን የጤና አይደለም፡፡ መዳፍዎ በድምቀት መቅላቱ ከድካም እና ከህመም ስሜት ጋር ተያይዞ ሲመጣ የጉበት በሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ በፍጥነት ሀኪም ማናገር ችግሩ ከመባባስ ያስቀራል፡፡  

ረጅም የቀለበት ጣት

የቀለበት ጣት ከአመልካች ጣት ከረዘመ በማህፀን ሳሉ ከፍ ላለ ቴስቴስትሮን መጋለጥዎን ያሳያል፡፡ ይህም ከፍ ያለ የወሲብ ስሜት እና የእድገት ተነሳሽነት እንዲኖር ቢያደርግም በሌላ በኩል ደግሞ አርትራይተስ የተባለውን የመገጣጠሚያ ችግር  ያሳያል፡፡ ይህ ከሆነ የጉልበትዎን ጥንካሬ ለመጨመር እግርዎን በማንሳት ጡንቻዎን ያዳብሩ፡፡ ሐኪም ማየትም እንዳለብዎ አይዘንጉ፡፡

የማያምሩ ጥፍሮች

ጥፍሮች ላይ የሚታይ አግድሞሽ መስመር ቀድሞ የነበረ ህመምን ወይንም የተመጣመነ ምግብ ጉድለትን ያሳያል፡፡ አንዳንዴም በጥፍር መቀጥቀጥ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ነገር ግን ተደጋግሞ የሚታይ ከሆነ ጤናዎን ለማሻሻል መሞከር ይኖርብዎታል፡፡ 

እንደ ማንኪያ ጎርጎድ ያለ ጥፍር በተለምዶ “ደም ማነስ” የምንለው ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ የጥፍር ጫፎች ቀይ ቡኒ መሆን በኩላሊት መታመም መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ 

 ቀዝቃዛ እግር

ከደም ዝውውር ጋር ተያያዥነት ያላቸው በሽታዎች በመጀመሪያ መታየት የሚጀምሩት በእጅ እና በእግር ዙሪያ ነው፡፡ ምክንያቱም ከልብ በጣም ርቀው የሚገኙ ቦታዎች ስለሆኑ ነው፡፡ከልክ ያለፈ የሚቀዘቅዙ እጅ እና እግሮች የተለያዩ ችግሮች ምልክት ሊሆኑ ስለሚችሉ በጊዜ መታየቱ አይከፋም፡፡

Total Page Visits: 1883 - Today Page Visits: 1

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *